በትግል ስም ትግልን መግደል – አ . ሰመረ

የአቶ ሰውየውን ጽሑፎች በዚህና በሌሎችም ድረ-ገጾች ላይ ስለሚያገኟቸው ያንብቡና እኒህ ወገናችን
በሚሉት ላይ በመጨመር ወይም በመደገፍ ካለያም የግል አስተያየትዎን ያስቀምጡልን
አቶ ሰውየው ከሕብረተ-ሰቡ  የሚሰነዘረውን ለመስማት ዝግጁ ነው።

ነገሬን በተረት ልቀድሰው ባገራችን አንድ አባባል አለ ይኸውም ሰውየው ማንን ታሸንፋለህ ቢሉት ሚስቴን አለ ይባላል ደካማነቷን አይቶ ማለት ነው እንደሱ ያለውንና የፈረጠመውን ጎረምሳ እንዳይል ፈርቶ ይህንን አባባል እኛም ዛሬ ኢሀደግን እየታገልን ነው የምንለውም የዚ ተረት ወራሽ ሆነን እንደ ወረርሽኝ በሽታ ተዛምቶብን ዋናውንና የሀገራችን ደመኛ እህአዴግን ከመታገል ይልቅ አቅም ያጣውንና ሊያገግምና ሊነሳ የሚጣጣረውን የህዝብ ወገን የሆነውን ድጋፍ የሚሻውን ደካማውን እየፈለጉ ጭራሽ ከበሽታው እንዳያገግም በተኛበት ሄዶ እንዳይነሳ ማድረግ ጀግንነት አድርገነው ደረታችንን እንነፋለን ይሄ ጀግንነት ወይም ወንድነት አይደለም ይልቁንም ይሄንን መሰል ድርጊት ፈጻሚውን ትንሽነትና እርካሽነት የሚያሳይ ጉልህ መስታወት ነው።
በቅርቡ በተደጋጋሚ በተለያዩ ድህረገጾች ላይ አቶ ሰውየው በሚል ስም የግለሰቦችን ስም እያነሳ በጣም የወረደና ዝቅ ባለ ክብረነክ ዘለፋዎችን ጽፎ ተመልክቼ በጣም አዝኛለሁ። እኚህ ሰው ብዙ ግዜ በምገባባቸው የውይይት መድረኮች ውስጥ እድል ገጥሞኝ ስገባ አደምጣቸው ስለነበርና አመለካከታቸውም ከኔ ከግል አመለካከት ጋር በብዙ መንገዱ ስለሚቀራረብ ለኚህ ሰው ትልቅ ከበሬታ ነበረኝ። አሁን ድርጅት በድርጅት ላይ እየተፈጠረ ተቃዋሚው ቡድን ከቀን ወደቀን እየደከመ እየተከፋፈለ በመጣበት ጊዜ በመሀከላችን ያለውን ልዩነት ለማጥበብና ለመሰባሰብ ጎንበስ ቀና እያልን በምንሯሯጥበት ወቅት ተቃዋሚ ነን በሚል ስም በአድራጎት ግን ኢሀዴግን ሊያግዝ የሚችል ነገር እየሰሩ ተቃዋሚውን ካለው ድክመት ላይ ይባስ የሚያዳክም የእርስ በርስ ሽኩቻን አጋኖና አልፎም ተፈጠረ ለሚባለው አለመግባባት እንዳይበርድ እያራገቡ ያለ የሌለ ነገር እየቀባጠሩ መዘባረቅ የሚያስተዛዝብ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። አለመግባባት ካለም ላለመግባባት ምክንያት ለሆነው ጊዜ ሰጥቶ ለችግሩ መፍትሄ መሻት በተገባ ነበር ያን ሳያደርጉ ተንደርድሮና ተቻኩሎ ነገሩ እንዳይበርድ ተጣድፎ ለነደደው እሳት ቤንዚን ማቀበል እጅግ የሚያሳዝን አቀራረብ ነው። ምነው እኚህ ግለሰብ ለተፈጠረው አለመግባባት አስታራቂ ሊሆን የሚችል ሀሳብ እንዳሁኑ ለመከፋፈልና ለማዳከም እንደሮጡት ለማስታረቁም በዚሁ ፍጥነትና ጉልበት አልሰሩበትም? ለማፍረስና ለመከፋፈል ሲሆን ምን አጣደፋቸው? ለግንባታ ሳይሆን ለማፍረሱ ብእራቸው ሰላ እነኚህ ተወቃሾች ዛሬ ቢያንስ ኢህአዴግን ባለ አቅማቸው እየታገሉ ያሉ ግለሰቦች እንደሆኑ እኔ እንደግለሰብ የምመሰክርላቸው ብቻ ሳይሆን ማንም ስራቸውንና ድርጊታቸውን ያየ ሁሉ የሚመሰክርላቸው ነው። ነገር ግን የህዝብ ወገን እንደሆኑ እያወቅን እኛ ያልነው ብቻ ካልሆነ እኛን ካላደመጡ በሚል ትምክህት ተነሳስቶ ይህን ያክል ወቀሳና ክብረነክ ባልተገባ ነበር ። ዛሬ ባለንበት አገር የኑሮውን ሁኔታ እያወቅን ያንን ሁሉ መስዋእትነት ከፍለው እየታገሉ ያሉን ግለሰቦች እንደማበረታታት በተቃራኒው ከፍ ዝቅ እያደረጉ ማራከስና መዝለፍ ታጋዮች ከትግል እንዲርቁ ለማድረግ የሚደረግ የውስጥ ስራ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ሊሆን ይችላል ብሎ ለመገመት ያዳግታል።
ኢህአዴግን በጠላትነት የፈረጀና ኢህአዴግን እታገላለሁ ከሚል አንድ ግለሰብ የሚጠበቅም አይደለምና ጸሀፊው ያላቸው አቋም ኢሀዴጋዊ እንጂ ኢትዮጵያዊና ወገናዊ አልመስል ብሎኛል።
ይህንን ተደጋጋሚ የሆነ ጽሁፍ ሲያወጡ በነገሩ አላሰቡበትም አልተጨነቁበትም ለማለትም አያስደፍርም ስለሆነም የኚህን ግለሰብ የፖለቲካ አመለካከት ቀደም ብዬ አደምጣቸው ከነበረውና ከአንደበታቸው ይወጣ ከነበረው ቃል ጋር እጅግ የተለየ ሆኖ በማየቴ እውን እኚህ ግለሰብ ያን ሁሉ ጊዜ ያልሆኑትን እንደሆኑ አድርገው ነበር የሚያቀርቡት? ያ ከሆነ በእውነት በማስመሰል ችሎታቸው ሳላደንቃቸው አላልፍም። ካልሆነ ግን መሰረተቢስ በሆነ የግል ፍላጎት ተነሳስቶ ዜጎችን ማዋረድ ባህላችን አይደለምና ጸሀፊው ልቦናው ሰጥቷቸው ወደህሊናቸው ተመልሰው ላደረጉት ስህተት ይቅርታ ጠይቀው ከትግሉ ጎራ ቢሰለፉ መልካም ነው የሚል አስተያየቴን እለግሳቸዋለሁ። ያን ማድረግ ቢያቅታቸው አንኳን ለሀገራቸው በሚደክሙና በሚለፉ ቡድኖችና ግለሰቦች መሀከል እየገቡ ቀና ሰዎችን እንዳይሰሩ ከማደናቀፍ ቢቆጠቡ ይመረጣል ይህንን መፈጸም ካልተቻላቸው ግን በትክክል ከየትኛው ወገን እንደሚያስፈርጃቸው ለጸሀፊው ልነግራቸው አይገባም ከኔ የላቁና ያወቁ ናቸው ብዬ አምናለሁና።
እዚህ ላይ አንድ ሳልጠቅሰው የማላልፈው ጉዳይ ቢኖር እኚህ ግለሰብ የሚደግፉት ድርጅት የሚወነጀልበት አንዱ ጸሀፊው በጽሁፋቸው የሚያንጸባርቁት አይነት የእኔ አውቅልሀልሁና የሁሉ ነገር ፈጣረና ወሳኝ እኛ ብቻ ነን የሚል ትምክህተኝነት ስለሆነ የሚወነጀሉበትን ሁኔታ ያጠናክረዋልና ምናልባት የሚደግፉትና እየታገልኩለት ነው ለሚሉት ድርጅት እውነተኛ ደጋፊው ከሆኑ ለድርጅታቸው አሳቢና ተቆርቋረ ከሆኑ ድርጅቱን እየጎዱት እንጂ እየጠቀሙት እንዳልሆነ እንዴት ተሳናቸው? ድርጅቱም የጸሀፊው አካሄድ ትክክል እንዳልሆነ አስገንዝቦ አቋም ሊወስድበትና አባላቱንም እንዲታረሙ ማድረግ የሚቻልበት መንገድ ካለ በጽሞና ሊያስብበት ይገባል።
በትግል ስም ትግልን ማዳከም በኢትዮጵያዊነት ስም ኢትዮጵያን መግደል በህዝብ ስም ህዝብን መበደል ሊያበቃ ይገባልና ወደ ህሊናችን ተመልሰን አገራችን ከወደቀችበት አዘቅት እናውጣት።
አ . ሰመረ
አድርባይና አስመሳይ ታጋዮች ይጋለጡ
ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ይኑር
አምላክ አገራችንን ይባርክልን

This entry was posted in Articles. Bookmark the permalink.

4 Responses to በትግል ስም ትግልን መግደል – አ . ሰመረ

Comments are closed.