ቅንነት !!

ከአባ ታቦር

 

አንዳንድ የሀገራችን ምሁራን፤ የታያቸዉን የጊዜዉን ችግር በተመለከተ፤ የተናገሩት የጻፉት ታሪካዊ ሰነድ በቋሚ ምስክርነት ይገኛል። ምሁራኑ ወያኔ ኢሕአዴግ የሚከተላቸዉን የጥፋት መንገዶች ሁሉ፤አንድ ጊዜ ቆም ብሎ እንዲመረምራቸዉ የሚያሳስቡ ናቸዉ። ነገር ግን ይህ መንግሥት ከቁብ የስገባቸዉ የምሁራን ምክር እስከ ዛሬ አልተገኙም።

አንድ ስሙን  የረሳሁት መምህር ፤ ከጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ጋር በአዲስ አበባ ዩንቬርስቲ የዉይይት መድረክ ላይ የተናገረዉ፤ ልቤን የነካዉ በመሆኑ፤ሁሌ ሳስታዉሰዉ እኖራለሁ።

ይህ ወጣት ምሁር፤ ጠቅላይ ሚንስትሩን በሚገባ ያጠና፤  እራሱን እንደ ትንሽ ትል በመቁጠር ዝቅ አድርጐ፤ በአንፃሩ አቶ መለስን ከፍ፤ ምሉ በኩለሄ የሆነዉን ሥልጣናቸዉን  በማጉላት፤ እንዲህ አለ። “…እባከዎ በተቻለ መጠን ቅን ይሁኑ፤ ቅንነት አይለየዎ።ይህች ሀገር በርስዎ እጅ ዉስጥ ነዉ ያለችዉ።ተስፋዋ እርሰዎ ነዎት” በማለት የሀገሪቱንና የሕዝቡን መከራ እንዲያቃልሉ፤ ለቅሶ የቀረዉ ልመና፤ አቀረበላቸዉ።ይህ ማሳሰቢያ ግን የአቶ መለስን ስሜት አለመንካቱ የሚገርም ነበር።በሀገር በወገን ከደረሰዉ ድቀት አኳያ፤ ከዚሀ ምሁር ማሳሰበያ ተነስቶ፤ እራሱን የማይመረምር አመራር ምን ይባላል?። ተልዕኮዉስ ምን ሊሆን ይችላል?።  (ይህን ታረካዊ ዉይይት በዩቲዩብ ይገኛል)

ከዚሁ ዩኒቨርስቲ የተነሳ አንድ ሌላ ወጣት ምሁር፤በሌላ ወቅት እንዲሁ ብርቱ ማሳሰቢያ አቅርቦላቸዉ ነበር። የተባለዉ ወጣት በትዉልድ ከኦሮሞ ጎሣ መሆኑን አረጋግጦ “ እርሰዎ መለስ ዜናዊና ፓርቲዎ፤ የብሔር ብሔረሰብን ጉዳይ ከሚገባዉ በላይ አጋናችሁ በማቅረብ፤የጋራ አባቶቻችን የደከሙለትን አንድነት በማናጋት ላይ ትገኛላችሁ” በማለት ምሬቱን አስምቶ እንደነበር እናስታዉሳለን። ይኸዉ ወጣት በመቀጠልም “የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳር አስከዳር ተፋቅሮና ተዋዶ፤ ተባብሮና ተጋብቶ፤ለዘመናት በዚህችዉ መሬት ላይ ኑሮአል።ዛሬ ሕዝቡን ለያይቶ ሆድና ጀርባ ማድረግ ጠቃሚ አይደለም” በማለት ዉጥረቱ እንዲላላ፤ፍቅር ሰላም በሀገሪቱ ላይ እንደገና እንዲመለስ፤  አስተያየቱን አቅርቦ አንደነበር እናስታዉሳለን። የዚህንም ምሁር አስተያየት፤መለስ ዜናዊ ከቁም ነገር ሳይቆጥሩት አልፈዋል።

         (የዚሀም ሰዉ ማሳሰቢያም በዩቲዩብ ይገኛል)

አንድነቱን በተመለከተ፤ኢሕአዴግ ያደረሰዉን በደል ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም እንዲህ ሲሉ አቅርበዉታል። “አባቶቻቸዉ ኢትዮጵያዉያን ነን ብለዉ የተዋጉና የሞቱ ሰዎች ልጆች፤ዛሬ ኢትዮጵያዉያን አይደለንም ብለዉ ተዋግተዉ ድል አግኝተዋል።ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸዉ ሌሎች ቡድኖችም፤ ለተመሳሳይ የመገንጠል ጦርነትና ድል እየተዘጋጁ ናቸዉ።ይህ  በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ነገር ነዉ” በማለት በአቶ መለስ አመራር በሀገሪቱ ላይ የደረሰዉን ጥፋት አሳይተዋል።

በዚህ መንግሥት አመራር፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሞት፤ከእስራት፤ከግርፋት፤ እንዲሁም ከእራብ ለመዳን ስደትን እንደመረጠ እንዲህ ሲሉ ግልፀዉታል።  “የተማሩት ሀገሪቱንና ሕዝቡን ከችግር ማጥ ዉስጥ ያወጣሉ ተብለዉ ተስፋ የተጣለባቸዉ ሁሉ፤ ወደ አዉሮፓና አሜሪካ ተሰደዱ።ከኀሊና ቁስላቸዉ ጋርም እንዲኖሩ ተገደዱ።በዚህ አዲስ ባህል ዉስጥ፤ ከኳስ ተጫዋቾች እስከ አምባሳደሮች፤ ሊቃነ ጳጳሳት ድረስ ገብተዉበታል” በማለት የአገዛዙን ጨካኝነት ቢጋልጡም፤ የአቶ መለስ መንግሥት ከጉዳይ አልጣፈዉም።  

            (ኢትዮጵያ—ከየት–ወዴት ገጽ 4- ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)

ይህ ሁሉ በሀገሪቱ ላይ የደረሰዉ ጥፋት፤ቅን አስተዳደርና ኃላፊነት የጐደለዉ የመለስ ዜናዊ መንግሥት፤ የምሁራንን ምክር ችላ በማለቱ ነዉ።ምሁራኑ አበክረዉ መለስ ቅን እንዲሆኑ የመከሩት፤ ዛሬ ለጀሮ የሚቀፈዉ ዓለም መሳቂያና መሳለቂያ ያደረገዉ የወገን ሰቆቃ እንዳይደርስ ነበር።ግን ምን ያደርጋል።የመለስ ዜናዊ አስተዳደር፤እንኳን ለጠቅላላዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀርቶ፤ቆምኩለት ለሚለዉ ለትግራይ ሕዝብ አልሆነም።ዛሬ ኢትዮጵያዉያን  በአራቱ ማዕዘን እየተሰደዱ ዓለምን አሰልችተዋል።እህቶቻችን ወንድሞቻችን ግፍ በሰፊዉ ከሚቀበሉበት አረቡ ዓለም ለመግባት፤በባሕር ሲጓዙ አብዛኖቹ ሰጥመዉ እንደሚቀሩ በየጊዜዉ የምንሰማዉ መርዶ ነዉ።በሰሀራ በርሀ በአሸዋ ተዉጠዉ ከሚቀሩት የተረፉት፤ በሲና ምድረበዳ በአረብ ምንደኛ በቁማቸዉ እየተበለቱ ወድቀዉ የሚቀሩት፤ ብዙ ናቸዉ።እረኛ ያጣዉ ወገናችን በየቦታዉ አደጋ ሲደርስበት፤የዓልም ሕዝብ ቢጮህለትም፤በመለስ ዜናዊ የሚመራዉ መንግሥት፤ ዓይኑን በጨዉ አጥቦ “ሳይጐልባቸዉ ሀገራቸዉን እየጣሉ የሚሄዱት፤ የደርግና የቀኃሥ መንግሥታት ናፋቂዎች፤ ነፍጠኞችና ኦነግዎች ናቸዉ” ይለናል።

በዓለም መድረክ፤ በታረኳና በጥንታዊ ባሕሏ ተከብራ የኖረችዉ፤በፍሪቃ አህጉር እንደ መሪና አንደ መመኪያ ትቆጠር የነበረችዉ ኢትዮጵያ ሀገራችን፤ በወያኔ ኢሕአዴግ ዘመን፤የእራብ፤የብጥብጥ፤የእስራት፤የስደት፤የሞት ማዕከል ሆና መገኘቷ፤ እኛን ልጆቿን ያሳዝነናል።

ታላቁ ገጣሚ  ደበበ ሰይፉ፤ ይህ የጥፋት ዘመን በሀገራችን እንደሚደርስ አበክሮ ታይቶት ኑሮ፤ እንዲህ ሲል አስቀምጦት አልፏል።

 

“……. ጽጌዎች  ደረቁ ንቦችሽ  አለቁ  ሰዎችሽ  ደቀቁ ፤

      መስክ  ላይ  ተኝተዉ  በድማ  ላይ ነቁ” ።

 

በየጊዜዉ የሚነሱ መንግሥታት፤“በሀገር ላይ የሚደርሰዉን ድቀት እናሶግዳለን እኩልነትን፤ ነፃነትን እናመጣለን” ብለዉ ይንደረደሩና፤ሥልጣን ሲጨብጡ፤ የባሱ ሆነዉ ይገኛሉ።የዚህ ምክንያቱ ከጅምሩ በቅንነት አለመነሳታቸዉ ነዉ። ወያኔ/ኢህአዴግ፤ደርግን አሶግዶ፤ዘረኝነትን፤ቂመኝነትን፤ምቀኝነትን፤ትዕቢትን ሳይከተል፤ በቅንነት ማስተዳደር ቢጀምር ኖሮ፤ ከዚህ ፈታኝ ጊዜ ላይ  አይደርስም ነበር።

 

ዛሬ መዉጫ ቀዳዳ ሲያጣ “በልማት ላይ ተሰማርቻለሁ፤ ልማታዊ መንግሥት ነኝ፤አትንኩኝ፤አታደናቅፉኝ”ይለናል። ልማት ጥናትን ይጠይቃል።  በጥናት ላይ ተደግፎ የማይከናዎን ልማት እርባና የለዉም።እራሱን መንግሥቱንና ሕዝቡን ማታለል ነዉ። በአባይ ላይ አንድ ትልቅ ግድብ ማቆም ማለት፤ ከሚጠይቀዉ ከባድ መዋዕለ ንዋይ ሌላ፤ በከባቢ አየር ላይ የሚያመጣዉን ጣጣ አለመገንዘብ ሞኝነት ነዉ።ከዚህ ሌላ በምዕራብ ኢትዮጵያ መሬትን ሸፍኖ የኖረዉና ዝናም የሚስበዉ ደን እየተመነጠረ መቃጠሉ፤ወደፊት በሀገራችን ላይ  የአየር መዛባት  እንደሚያስከትል ግንዛቤ አለመወሰዱ እጅግ ያሳዝነል።ያስቆጫል። በጋምቤላ፤ በቤኒሻንጉል፤ በወለጋ፣ በኢሉባቡር፣ በከፋ፣ በጐምጐፋ፣ መሬት በርካሽ ዋጋ እየተቸበቸበላቸዉ፤በኢንቬስተር ስም፣የዉጭ ሀገር ሰዎችና ድርጅቶች፤ሀገሪቱን በከፊል ተረክበዋል።ተወላጁን በግፍና በጭካኔ በማፈናቀል ላይ ይገኛሉ።

 

ይህ ሀላፊነት የጐደለዉ ደርጊት፤በተከዜ ሸለቆም በሰፊዉ ቀጥሎአል። ሰኳር  ለማምረት ሲባል፤ ለብዙ አመት በደን ተሸፍኖ የኖረዉ የወልቃይት፤ ጠገዴ የጠለምት፤ መሬት እየተመነጠረ ነዉ።በሀገራችን የታወቀዉ ዋልደባ ገዳም ሳይቀር በመታረስ ላይ ይገኛል። በዉስጡ የነበሩት መነኮሳት እንዲበተኑ ተገደዋል።የጎንደር ሕዝብ ቦታዉ ድረስ በመሄድ የዕመነታችን ምልክት የሆነዉ ገዳማችን አይነካብን ቢልም፤ቦታዉን በወታደር በማጠር ጥፋቱ ቀጥሏል።

 

በዘላንነት የሚኖረዉ የአፋር ሕዝብ፤ከመሬቱ በመፈናቀል ላይ ይገኛል።ዉሀ ገብ ለምለም መሬቱ ለሰኳር አገዳ ተክል ስለተመደበ፤ሕዘቡ መንጋዉን እየነዳ ወደ ደረቁ መሬት እንዲሸሽ እየተገደደ ነዉ።የዚህ ሕዝብ ሕይዎት ከአዋሽ ወንዝ ጋር የተሳሰረ ሆኖ ሳለ፤ለልማቱ ሲባል ከዚያ እንዲርቅ መደረጉ፤የግፍ ግፍ ነዉ።

 

የልማት አጋሮቻቸዉ የሆኑት ቻይናዎቹ፤ሥርዓት ያለዉ ልማት በኢትዮጵያ  ተከናዉኖ ማየት ይፈልጋሉ።ይህ ዉቂዉ ደብለቂዉ የበዛበት ልማት፤ያለበቂ ጥናት እንዳይከናወን መክረዋል ይባልል።እራሳዉ ቻይናዎቹ በልማት ስም አገራቸዉን ያለ በቂ ጥናት ግልብጥብጡን አዉጥተዉ፤ ዛሬ ሊመልሱት በማይችሉት የአየር ጠባይ ለዉጥና ፖሉሽን እየተመቱ መሆናቸዉን፤ ሳይደብቁ “እኔን ያየህ ተቀጣ” በማለት መክረዋቸዋል ይባላል።ግን በእነ አቶ መለስ ቤት ቅንነት ስለሌለ፤ይህንም ቁምነገር ችላ ብለዉ አልፈዉታል።

 

ወያኔ ኢሕአዴ በድል በገባ በሶስተኛዉ አመት ላይ፤ ለሥራ ጉዳይ አርሲ ክፍለ ሀገር፣ፋሲል አዉራጃ፤ ጐሎልቻ ከሚባል ወረዳ ሄጄ ነበር።ያን አካባቢ ቀደም አድርጌ፤ በቀኃሥ ዘመን አዉቀዋለሁ።አዉራጃዉ ለብዙ ዘመን መንግሥትና ሕዝቡ ሲጠብቀዉ በኖረ ደን የተሸፈነ ነበር።ቀጥ ብሎ የወጣ ዝግባና ጥድ አይን እስከሚታክት ድረስ ለማየት ይቻል ነበር።ዉፍረቱ እርዝመቱ ከዚህ አሜሪካ ሀገር በካሊፎርንያ “ሬድ ዉድ” የሚባለዉን አይነት ይመስላል።ይህን መንሥትና ሕዝብ ሲንከባከበዉ የቆየ ደን፤ የወያኔ ባለዜዎች እየጨፈጨፉ እየሰነጠቁ ወደ ሰሜን ጫኑት።የገጠሩ ሕዝብ እያለቀሰ “እግዚኦ የመንግሥት ያለህ “ ቢል የሚሰማዉ አልነበረም።እነዚህ የዘመኑ መሳፍንት፤ ባልተወለደ አንጀታቸዉ፤ ሰዉንም ዛፉንም ጨፍጭፈዉ፤ አዉራጃዉን በትንሽ ጊዜ ዉስጥ አራቆቱት። ነፍጠኛዉ ያደገበት የተወለደበት ቦታ አሳዝኖት በሙሾ፤

 

      

         “ አገሬን ጐሎልቻን ብዞረዉ ብዞረዉ ፤

           ፋሲል አዉራጃንም ብዞረዉ ብዞረዉ

           አገሬ ጭላሎን ብዞረዉ ብዞረዉ፤

           ድንጋዉ ብቻ ቀርቷል የማይናገረዉ”

 

በማለት አለቀሰለት።

 

የገጠሩ ሕዝብ የበሬ ግንባር የምታክል መሬት ታድሎታል።ያችኑ እያገላበጠ አርሶ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ይገፋል።መንግሥት ነኝ የሚለዉ ኃይል መሬትን እስከ ግሳንግሡ ጠቅሎ በእጁ አድርጓል። ያ አልበቃ ብሎት ማዳበሪያ በዱቤ እንዲገዛ ገበሬዉን ያስገድዳል።የማዳበሪያ ዋጋ ከብዶት መክፈል ያቃተዉ መስኪን ገበሬ፤ በሬዉን እስከመሸጥ ይደርሳል። የበሬዉ ዋጋ ማዳበሪያዉን ካልሸፈነ መሬቱን አስረክቦ ይሰደዳል።

 

የወያኔ ጀሌ በልጅነቱ “መሬት ላራሹ” እያለ ወትዉቶ ወትዉቶ፤ ዛሬ ሥልጣን ሲጨብጥ፤የከተማና የገጠርን መሬት ነክሶ ይዟል። የኃይሉ ምጭም አድርጐታል። በዚህም የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደ ሰም አቅልጦ እንደ ብረት ቀጠቅጦ ለመግዛት አስችሎታል።

 

 

        “ የገጠሩ መሬት፤

         የመንገሥት ተብሎ፤ ያራሹ እጅ ካጠረ፤

         የገበሬዉ መብት፤በየምክንያቱ ከተቦረቦረ ፤

          

         መች እራብ ይጠፋል ከዉድ ሀገራችን

         ቅንነት ባነስዉ ከይሲ አመራራችን።                                     

           

                                    

    

         ኢትዮጵያ በልጆቿ ብርቱ ተጋድሎ ለዘልዓለም ትኖራለች !       

                       

                         abatabor@gmail.com

 

 

 

 

 

 

 

  

This entry was posted in Articles. Bookmark the permalink.